(ክንፉ አሰፋ አምስተርዳም)
አሜሪካዊው ደራሲ ማርክ ትዋይን በአንድ ጽሁፉ ላይ፣ “የሰጥቶ መቀበል ዲፕሎማሲ ሲባል አንድ ሰጥቶ አስር የመቀበል መርህ ነው” (The principle of give and take is the principle of diplomacy – give one and take ten) ብሎ ነበር፡፡ ጸሃፊው ይሕን ሲል የተደራዳሪዎችን የሃይል ሚዛን ተንተርሶ የሚደረገውን ያልተመጣጠነ ስምምነት ለመተቸት እንደሆነ እንጂ በእኩል ሰጥቶ መቀበልን ለመንቀፍ እንዳልሆን ግልጽ ነው፡፡ ያልተማጣጠነ የሃይል ሚዛን ባላቸው ቡድኖች መካከል የሚፈጸም ስምምነት ከቶውንም ለሁለቱም ወገኖች እኩል ሊሆን አይችልም፡፡
ሰጥቶ መቀበል (Give and Take) ዲፕሎማሲ በአብዛኛው የሚነገረው በእስራኤልና በፍልስጤም ችግር ዙሪያ በሚደረጉ ድርድሮችና ስምምነቶች ላይ ነው፡፡ አደራዳሪዎቹ Land for peace ይሉታል፡፡ እስራኤል መሬት ሰጥታ ለዘመናት ያጣችውን ሰላም መቀበል የሚደረግ አንጻራዊ የእኩዮሽ ስምምነት ነው፡፡ ይህ ስምምነት ሁለቱንም ስለሚያስር የሃይል ሚዛን በጥቂቱም ቢሆን በሚያዘነብለው በእስራኤል ላይ ትልቅ ጫና ሲፈጥር ይታያል፣ የሃገርና የሕዝብ ሰላም ከመሬት ይበልጣልና፡፡
ኢህአዴግ ሰራዊቱን፣ ደህንነቱን፣ ፖሊሱን፣ ቢሮክራሲዉን፣ መገናኛ ብዙሃኑንና ከሁሉም በላይ የሃገሪቱን ሃብት ሙሉ በሙሉ በተቆጣጠረበት ሁኔታና፣ የፍትህ ስርዓቱ በመለስ ዜናዊ ብቻ በሚታዘዝበት ምድር በእኩዮሽ ተስማምቶ ለሁሉም ወገኖች ገዢ የሆነ ስምምነት መፈራረም አይታሰብም፡፡ ከሆነም እነፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም እንደሚነግሩን አቶ መለስ ተለውጠዋል፡፡ የእስካሁኖቹ ተመክሮዎችም የሚያሳዩን ግን ኢሕአዴግ በሕግ ሽፋን ሲያታልል ብቻ ነው፡፡
ጥቂት ስለተፈረመው የስነ-ምግባር ሰነድ
አቶ መለስ፣ ኢንጅ. ሃይሉ፣ ልደቱና አየለ ሰሞኑን የተፈራረሙት የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ የሥነ ምግባር ደንብ ሰነድ ያካተታቸው አንቀጾች ግልጽ ያልሁኑና በህግ ተርጓሚውም ሆነ በህግ አስፈጻሚው በሚመች መልኩ ሊተረጎሙ የሚችሉ መሆናቸውን የህግ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ አንዳንዶቹ አስቂኝ ይመስላሉ፣ ነገር ግን ለገዢው ፓርቲ ትልቅ ትርጉም የሚሰጡና የተጠኑ ድንጋጌዎች ናቸው፣ ምርጫዎች ትክክለኛ ሂደትና ውጤት በፀጋ መቀበል ያንን በቁርጠኝነት ማረጋገጥ ከሚለው እስከ አስገራሚው “መራጮችን ያበሳጨ”- የሚሉት በገዢው ፓርቲ እንደፈለገው የሚተረጎምና የተቃወሚው (የተሸናፊው) ወገን የመተቸት መብት በሚነፍጉ አንቀጾች የተሞላ ነው፡፡ያንን የሚያደርግም ከባድ ቅጣት እንደሚጠብቀው ይገልጻል፡፡ ለግንዛቤ ያህል የሚከተሉትን አንቀጾች ተመልከቱ፣
-
ፍርሃት፣ ሁከት መፍጠር እና ማንኛውንም የምርጫ እንቅስቃሴ ማስተጓጎል፣
-
በምርጫ ቦርዱ ወይም በምርጫ አስፈፃሚዎች ገለልተኝነት ጣልቃ የገባ፣ መደለያ ወይም የተስፋ ቃል በመስጠት አንድ ሰው ተግባሩን እንዳያከናውን ያደረገ፣ የምርጫ ዘመቻውን ሰላም የሚያናጋ ወይም ግጭት የሚቆሰቁስ ወይም ስም የሚያጠፋ ወይም አመፅ የሚጋብዝ ወይም ስጋት የሚፈጥር ንግግር ያደረገ፣
-
በይፋም ሆነ በስውር አመፅን የሚቀሰቅስ ወይም የሚያስፈራራ ቋንቋ ይዘት ያለው በራሪ ወረቀት፣ የዜና መጽሔቶች ወይም ፖስተር ያሰራጨ በምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት በህዝቡ ላይ የፍርሃት እና የጭንቀት ሁኔታ የፈጠረ፣
-
የድምፅ አሰጣጡ ሂደት ሚስጥራዊ እንደማይሆን የሀሰት መረጃ የሰጠ፣
-
የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ወይም የምርጫ ውጤት አገላለፅ፣ የመራጮች ወይም የፓርቲዎች መብት ወይም ማስመሰል አስመልክቶ ክልከላዎች የሚጥሱ ድንጋጌዎች የማያከብር ወይም ሐሰት መሆኑን እያወቀ ወይም እውነት ስለመሆኑ በቂ ምክንያት ሳይኖረው ንግግር የሚያደርግ ሰው፣
-
ምርጫን ለማወክ ወይም እንዳይካሄድ ለማድረግ ወይም በምርጫው ሂደት ወይም ውጤት (out come) ላይ ጫና ለመፍጠር በማሰብ ጥላቻን (hostility) ወይም ፍርሀትን የሚያሰፍን ወይም በምርጫው ሂደት ወይም በምርጫው ውጤት ላይ ጫና የሚፈጥር የሐሰት መረጃ ያሳተመ፣…
ከላይ የተጠቀሱትን አንቀጾች ወይንም አንዱን አንቀ የተላለፈ እንግዲህ ከባድ የገንዘብ መቀጮና እስራት እንደሚጠብቀው ሰነዱ ይደነግጋል፡፡ ከተፈራራሚ ቡድኖቹ የሚነገሩት “ሰጥቶ-መቀበል” እና “ታሪካዊ ሰነድ” የሚሉት ሰነድ ነው እነዚህን ማስጠንቀቂያዎች ያካተተው:: እነዚህን ማስጠንቀቂያዎች ተፈጻሚ ያሚያደርገው የፖሊስና የፍትህ አካል ደግሞ የሚቆጣጠረው ኢሕአዴግ ነው፡፡
ወቅቱ አሁን ለምን ተመረጠ
ኢሕአዴግ ከተሸነፈበት ከ 1997ቱ ምርጫ በኋላ አቶ መለስ ዜናዊ ከቢቢሲ ጋዜጠኛ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ “We took a calculated risk” ሲሉ ነበር በወቅቱ የፖለቲካውን ምህዳር ለቀቅ ማደረጋቸው ያመጣባቸውን አደጋ በቁጭት የገለጹት፡፡ አሁን ጨርሶ የተዘጋው የፖለቲካ ምሕዳር ትንሽ እንኳን ገርበብ ቢል ኢሕአዴግ በምርጫ ሊያሸንፍ እንደማይችል የሚያመለክት ጥቆማ ነው፡፡ በየትኛውም መስፈርት ቢመዘን ኢሕአዴግ እንኳን ሊመረጥ ለምርጫ መቅረብ የማይችል – የቀድሞ አባላቱ እንደሚሉት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የማይጠቅም – የበሰበሰ ድርጅት ነው፡፡
ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳይ ሃላፊ የሆኑት ጆኒ ካርሰን በኬንያ የፖለቲካ ለውጥ (reform) አሻፈረኝ ባሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ የቪዛ ማእቀብ መጣላቸው የአፍሪካ አንባገነኖችን እንቅልፍ ነስቷቸዋል፡፡ የኦባማ አስተዳደር ከምስራቅ አፍሪካ አይኑን የጣለው በኢትዮጵያ ለይ መሆኑን በአቶ መለስ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ለዚሕም ራሳቸውን በሚጠቅም መልኩ ካሁኑ መዘጋጀት ነበረባቸው፡፡ ይህ ገና በተግባር እንኳን ያልተፈተነ ስምምነት ለፖለቲካ መነገጃም እየዋለ ነው፡፡ አቶ ስዮም መስፍን ከሂላሪ ክሊንተን ጋር ባላፈው ሳምንት በዋሺንግተን ዲሲ ሲገናኙ የተናገሩት ትልቁ ለውጥ ይኸው ስምምነት መሆኑን መገናኛ ብዙሃን እየነገሩን ገልጸዋል፡፡
አለም-አቀፍ ቀውስ ቡደን (International Crisis Group) በቅርቡ ባውጣው ዘገባ ምርጫ 2010ን ተከትሎ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝባዊ አመጽ ሊነሳ እንደሚችል በጥናት በተደገፈ መረጃ ማቅረቡ ሌላው የአቶ መለስ ቡድን ራስ ምታት ሆኗል፡፡ አቶ መለስ ይህንን የለውጥ ጥያቄ በተቻለው ሁሉ ማስወገድ አሊያም መቀነስ አለባቸው፡፡
አቶ መለስ ኢትዮጵያ በአኢኮኖሚ ከፍተኛ አድጋለች እያሉ በተደጋጋሚ ምእራቡን አለም ለማሳመን ቢሞክሩም 12 ሚሊየን የሚሆን ሕዝብ ለርሃብ ተጋለጠ የሚለው ዜና ድንጋጤ ውስጥ ከቷቸዋል፣ የሕዝቡን ትኩረት ከዚሕ ላይ ማንሳት አለባቸው፡፡
ወደ ኢንጂነር ሃይሉ ሻውል ስንሄድ ደግሞ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ መሪነታቸው ቀድሞ እንኳን ከሜዲያውና ከዲፕሎማቶች ያገኙ የነበረውን ትኩረት አጥተው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ታዛቢዎች እንደሚሉት ሃይሉ ሻውል የስምምነቱ ጭብጥ እና እንድምታ ላይ ትኩረት የሰጡት አይመስልም፡፡ የሳቸው ፍላጎት የስምምነቱ መስራች አባል ሆኖ ሌሎቹ ላይ በበላይነት ተፈጻሚ ማድረጉ ላይ ብቻ ነው፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም የስምምነቱን ሰነድ አቶ ሃይሉ እንዳላነበቡት ነው የሚናገሩት፡፡ ይህ ከሆን ብዙም አይደንቀንም፣ ኢንጂነሩ የቅንጅትን ማኒፌስቶ ሳያነቡት ያን ግዙፍ ፓርቲ ይመሩ እንደነበር ገሃድ ነው፡፡ አንድ ወቅት ከቪኦኤው አዲሱ አበበ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ስለዚሁ ጠይቋቸው “እሱን በኪሴ ይዤ አልዞርም!” ነበር ያሉት፣ ነገሩ መያዝ የነበረበት በኪስ ሳይሆን በአእምሯቸው ነበር፡፡ ማኒፌስቶውን ከአእምሯቸው ቢያኖሩት ኖሮ እነዛ ስህተቶችን ባልፈፈጸሙ!
ከመለስ ዜናዊ ጋር መጨባበጡን ይሆን እንደ መቀበል የቆጠሩት? ኢንጅነር ሃይሉ ‘ከመለስ ዜናዊ ጋር ካልሆነ ከሌሎች የኢህአዲግ ባለስልጣናት ጋር አአልጭባበጥም!’ ማለታቸውን የዜና ምንጮች ከኢትዮጵያ ጠቆም አድርገዋል፡፡ እናም አቶ መለስ ለሕክምና ብራስልስ ከሄዱበት እስኪመለሱ መጠበቅ ነበርባቸው፡፡ ይኽ ከፕሮቶኮል አንጻር ተገቢ ሊሆን ይችላል:: ከፋሽሽቶች ጋር መጨባበጥ ግን በራሱ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ የፕሬዚዳንት ሬገን ልዩ መልእክተኛ የነበሩት ዶናልድ ረምስፊልድ እ.ኤ.አ. በ1983 ዓ.ም. ከ ሳዳም ሁሴን ጋር ባግዳድ ላይ መጨባበጣቸው በአለም የመገናኛ ብዙሃን በእጅጉ ተወግዘው የሬጋን አስተዳደርና ፓርቲያቸው ዋጋ ከፍሎበታል፡፡ ውግዘቱ ካለምንም ምክንያት አልነበረም፡፡ በወቅቱ ሳዳም ሁሴን በሰብአዊ መብት ረገጣና በአገር ሉአላዊነት ላይ በሚፈጽሙት ጥፋት ተጠያቂ ነበሩ፣ አንዳንዶች እንዲያውም ይህንን ድርጊት በ1938 በሙንሽን ላይ ሂትለርና የእንግሊዙ አቻቸው ቻምበርሊን ያደረጉት መጨባበጥ ጋር አመሳስለውታል፡፡
ከምርጫ 1997 በኋላና ከዚያም በፊት በአቶ መለስ ትእዛዝ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እንዲገደሉ፣ አሊያም አካለ-ስንኩል እንዲሆኑ ተደርጓል፣ በፖለቲካ እምነታቸው የሚታሰሩት ዜጎች ቁጥርም በሺዎች ይቆጠራል፣ ይኽንን ጉዳይ ያላነሳ ስምምነት ላይ መፈራረምና – ስምምነቱን ‘ሰጥቶ መቀበል’ ብሎ ማወደስ ከአንድ ለፍትህ ከሚታገል ወገን ማየት በእርግጥም ያስደነግጣል፡፡
የመምረጥና የመመረጥ መብትን አንድ ፓርቲ የሚሰጠንና ሌሎች የሚቀበሉት ጉዳይ አይደለም፡፡ ኢንጅነር ሃይሉ፣ “በፈረንጆች ኩርኩም” ተቀበልነው ያሉት ያንን ከሆነ ለምን ለመኢአድ ኮርኳሚና አስገዳጅ እንዳስፈለገ ግልጽ አይደላም፣ ምክንያቱም የሃገሪቱ የበላይ ሕግ የሆነው ሕገ-መንግስት – ይህንኑ መብት ይደነግጋል፡፡ ከህገ-መንግስቱ በሚጻረር መልኩ “ይህን አታድርግ… ፣ ካደረግክ ጥቀጣለህ..” የሚል ስምምነት ላይ ተፈራርመው ከመጨባበጣቸው ውጪ የተቀበሉት ምን ንደሆነ አላወቅንም፡፡ ተቀበሉ ልንል የምንችለው ቅንጅት አውጥቷቸው የነበረውን ባለስምንት ነጥብ አቋም ለይ ቢፈራረሙና ቢያንስ በመኢአድ አባልነታቸው ታስረዋል ካሉት 600 የፖለቲካ እስረኞች ሲፈቱ፣ የተዘጉት ቢሮዎቻቸው ሲከፈቱ… ወዘተ ነው፡፡ ከስምንቱ የቅንጅት ቅድመ-ሁኔታዎች ቢያንስ “የምርጫ ቦርድ ገለልተኛ መሆን” የሚለው በአቶ መለስ ተቀባይነት ቢያገኝ ኖሮ ወይንም ቢካተተ ኖሮ ኢንጅነር ሃይሉ አንድ ነገር ተቀበሉ እንል ነበር፡፡
አብዛኞቹ የፖለቲካ ታዛቢዎች እንደሚሉት፣ ኢንጅነር ሃይሉ ሻወልና ፓርቲያቸው በህገ-መንግስቱ የተደነገገውን መብታቸውን ጭምር ለኢሕአዴግ አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ የተቀበሉት ግን ምንም ነገር የለም፡፡ ልደቱና አየለ ጫሚሶ እዚህ ውስጥ አይገቡም፣ ሁለቱ የህዝብን አደራና የህዝብን መብት፣ ለጥቅም የለወጡ ፣ ስለዚህ ሁለቱም መብታቸውን ሰጥተው በስውር ገንዘብ ተቀብለዋል፡፡
በጣም የሚያስገርመው ደግሞ ኢንጅነር ሃይሉ ባልተጠበቀ ሁኔታ ስምምናቱን መፈራረማቸው ሳይሆን የ2010 ምርጫ ውጤት ጥሩ እንደሚሆን ያለ ጥርጥር ከውዲሁ መናገራቸው ነው፡፡ ለምርጫው የቀረው ጊዜ 6 ወር ስለማይበልጥ ይሕንን በቅርብ የምናየውና የምንታዘበው ጉዳይ ነው፣ ግና ሃይሉ የተቀበሉት አሁን ይሁን ከምርጫው በኋላ ያለውን ውጤት ግልጽ አላደረጉትም፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ አለም አቀፉ ህብረተሰብ እንደሚያውቀው በነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ኢህአዴግ ተወዳድሮ ከቶውንም አያሸንፍም ሊያሸንፍ አይችልም፡፡ የብዙዎች ግምት ግን ኢህአዴግ የሚበቃውን ወንበር ከወሰደ በኋላ የቀረውን የፓርላማ መቀመጫ በኮታ ለልደቱ፣ ለአየለና ለኢንጅነር ሃይሉ ይሰጥ ይሆናል የሚል ነው፡፡ ፓርላማውን ለማድመቅና ለነ ተሾመ ቶጋ አይነቶቹ መቀለጃ ለመሆን! ይኽ ከሆነ ደግሞ መኢአድ 10 ሰጥቶ 0 መቀበልን ተገበረው ማለት ነው፡፡… ማርክ ትዋይን ያለው አንድ ሰጥቶ አስር የመቀበል ባልከፋ ያሰኛል!
Twitter
Mister Wong
Digg
Del.icio.us
Slashdot
Furl
Yahoo
Technorati
Newsvine
Googlize this
Blinklist
Facebook
Wikio